ፕሮፖጋንዳ ከየትኛዉም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የበለጠ ሀይል ያለዉ እና አንድን ዒላማ ያደረገበትን የህብረተሰብ ክፍል ሊያከሽፍ እና መልሶ ለራሱ ዓላማ መጠቀሚያ ሊያደርግ የሚችል መሳሪያ ነዉ።
ዉጤታማ ፕሮፖጋንዳ ማለት ይህ ዒላማ የተደረገበት የህብረተሰብ ክፍል የያዘዉ አቋም አሊያም እዉነት ነዉ ብሎ የተቀበለዉ ሀሳብ በፕሮፓጋንዲስቱ ጫና ያልመጣ መስሎ ሲሰማዉ እና እራሱ አንፃራዊ ሁኔታዎችን መርምሮ የደረሰበት መደምደሚያ እንደሆነ ሲገምት ነዉ።
ይህን አይነት "ዉጤታማ" የፕሮፓጋንዳ ስትራቴጂ ለመተግበር ፕሮፓጋንዲስቱ በቅድሚ የዚህን ዒላማ ያደረገበትን የህብረተሰብ ክፍል ማንነት እና ምንነት ያጠናል፤ ደካማ እና ጠንካራ ጎኑን ይፈትሻል፤ የመረጃ ምንጬን፣ መረጃዉን የሚያገኝበትን መንገድ እና መረብ ይመረምራል።
ከዚህ ጥናት በኃላ በምን መልክ ምን መረጃ እንዴት ማቅረብ እንዳለበት እና ለምን ዓላማ ይህ ሊሆን እንደሚችል ይለያል።
በተለያየ መንገድ ማለትም በመጽሀፍ፣ በምርምር መልክ፣ በትምህርት፣ በመገናኛ ብዙሀን፣ እናም በግለሰብ ደረጃ ፕሮፖጋንዳ ሊዛመት ይችላል
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣዉ አሉታዊ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ረቂቅነትም ከዚህ የቆዬ ጥናት የመነጨ ነዉ።
የሚቀርብልህን መረጃ መጠየቅ ካልቻልክ፣ በጥቅሉ እዉነት ነዉ ብለህ ከተቀበልከዉ ተሸንፈሀል። እርግጥ ነዉ ትምህርት በከፍተኛ ደረጃ ንግድ እየሆነ በመጣበት በአሁኑ ዘመን ለእንደኛ ላለ ተራ የህብረተሰብ ክፍል ሁሉንም ለመመርመር የሚያስችል ማስረጃ ለማግኘት እና ይህንንም መንገድ ለመከተል ጊዜም ገንዘብም ይጠይቃል።
ነገር ግን መሰረታዊ የመጠየቅ ክህሎት ካዳበርክ ጉዳዩን ከስረ መሰረቱ ባትደርስበትም እንኳ በጥርጣሬ እንድትመለከተዉ ይረድሀል።
ለምሳሌ ያህል በኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ዉሱን የምታምነዉን አቋም በጥቅሉ እንዉሰድ፣ ይሄን አቋምህን እንዴት እና በምን መረጃ ላይ ተመስርተህ ልትደግፍ ቻልክ? ለዚህ አቋምህ እዉነት ያልካቸዉን የመረጃ ምንጮች ከየት እና በምን መንገድ አገኘህ? እነዚህ የመረጃ ምንጮችህ የኋላ ታሪክ ምንድን ነዉ? ይህ የያዝከዉ አቋምህ ከሌላዉ ኢትዬጵያዊነትን በተመለከተ ካለዉ መሰረታዊ አቋምህ በምን መልኩ ይቃረናል ወይንስ ይታረቃል? ይሄን ፕሮፖጋንዳ በግልጽም በሽፋንም የሚያቀብሉህ አካላት የወሰድከዉን አቋም ተከትለህ ምን እንድታደርግ ነዉ የሚፈልጉት ? ይሄን መጠየቅ እና መመርመር ከቻልክ አይንህ እየተገለጠ እና እየሆነ ያለዉን እየተረዳህ ትሄዳለህ።
የሚባለዉ እና በመሬት ላይ ያለዉን ነገር አነፃጽሮ እየሆነ ያለዉን መለየቱ ላይ ነዉ ቁም ነገሩ።
ሰላም አሰፍናለሁ ያለህ ሁሉ የሰላም ዘብ ላይሆን ይችላል፤ የዴሞክራሲ ማማ ነኝ የሚልህ ሀገር እና መንግስት ሁሉ የሚለዉ እና እየሆነ ያለዉ የተለያየ ነገር ሊሆን ይችላል፤ አንድነትህን ላስጠብቅልህ የሚልህ ሁሉ የበለጠ ሊበትንህ ይችላል። አሊያም ነጻነት አመጣልሀለሁ ወይንም አመጣሁልህ ያለህ ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የባርነት ቀንበር ሊያጠልቅልህ እያመቻቸህ ሊሆን ይችላል። ነፍሱን ለመታደግ እርዳታ የሚያስፈልገዉ ህዝብ እና መንግስት የቁስ እና የገንዘብ እርዳታ ለጋሽ ነኝ እያለ ሀገርህን ሊዘርፍህ ሲዳዳ ካመንክዉ ችግር ነዉ።
አንተ በትክክል ምንድን ነዉ የምትፈልገዉ? ይሄ ፍላጎትህ እንዴት እና ከየት መጣ? ፍላጎትህ እና ተግባርህ እንዴት ይግባባል? ይሄን መርምር እንጂ ጠበቃህ ነኝ ያለህ ሁሉ ለክስ እያመቻቸህ እንዳይሆን ተጠንቀቅ።
ፕሮፓጋንዳ ሁሉ መጥፎ አላማ አለዉ ሊባል ባይችልም እንዲህ ኢትዬጵያ ላይ እንደተቃጣዉ ያለ እንደ ምስጥ ውስጣችንን ሰርስሮ ለመጣል የደረሰ አደገኛ ነገር የለም።
እጅግ አደገኛ የሚያደርገዉ ደግሞ በአጠቃላይ በህልዉናችን የመጣ እና ሳናዉቀዉ የዚኽዉ የህልዉናችን ማጥፊያ መሳሪያ እና ሰለባ መሆናችን ነዉ።
የፕሮፖጋንዲስት አላማ አዉቀኽዉም ሆነ ሳታዉቅ እንድትከተለዉ እና ለፈለገዉ ግብ መሳካት መሳሪያ እንድትሆነዉ ማድረግ ነዉ። ከዚያ በኋላ አንተ ላይ ስለሚፈጠር ተፅዕኖ ሀላፊነት አይወስድም።
ይሄንን የቆዬ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመቋቋም የግድ ተቋማዊ የሆነ የካዉንተር ፕሮፖጋንዳ እና ኢንዶክትሬኔሽን ማዕከል በግልጽም ሆነ በሽፋን ሀገሪቱ ማቋቋም ያስፈልጋታል። ምክንያቱም በግለሰብ ደረጃ ይሄን ሁሉ ከብረት የከበደ የፕሮፖጋንዳ ናዳ ተቋቁሞ እና ተከላክሎ መቆም አይቻልም።